ምሥጢረ ጥምቀት - በማን ስም ልንጠመቅ ይገባል
ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰዎች የእግዚአብሔርን ልጆች ይሆኑ ዘንድ በሥላሴ ስም ታጠምቃለች፡፡ ይህም ጌታ ራሱ ለሐዋርያቱ ‹‹ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ያጠመቃችኋቸው፡፡›› (ማቴ. 28÷19) ብሎ የሰጠውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ደም ከተመሠረተችበት ዘመን አንስቶ በሥላሴ (በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ) ስም መጠመቅ የድኀነት በር ቁልፍ መሆኑን ስታስተምርና ተግባራዊ ስታደርግም ኖራለች፡፡
ይህንን የወንጌል ቃል የሚያጣምሙ መናፍቃን በኢየሱስ ስም ብቻ መጠመቅ አለብን እንጂ በአብ፣ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ የለብንም ይላሉ፡፡ ለዚህም ማስረጃ አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት የሐዋርያው የቅዱስ ጴጥሮስን አነጋገር ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ ለተሰበሰቡት አይሁድ የምሥራቹን ቃል ድምጹን ከፍ አድርጐ ባሰማቸው ጊዜ ልባቸው ተነካ፡፡ ስለዚህም ‹‹ምን እናድርግ›› ብለው ሊያደርጉት የሚገባቸውን እንዲነግራቸው ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ንስሐ ግቡ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ አላቸው›› (የሐዋ ሥራ 2÷38)፡፡
ሐዋርያው ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ›› ብሎ ማስተማሩ ለምን ነበር? ለምን ጌታ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ ያለውን ተከትሎ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ተጠመቁ አላለም? የሚል ጥያቄ ለሚያነሣ ሁሉ ምክንያቱ እንደሚከተለው ነው፡፡በበዓለ ሃምሳ ከየሃገሩ የተሰበሰቡት አይሁድ ከጥንት ጀምሮ በነቢያት አንደበት ይወርዳል ይወለዳል እየተባለ የተነገረለትን መሲሕን ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ ሐዋርያውም ያ የተስፋው ቃል ዛሬ መፈጸሙንና በተስፋው ቃል መሠረት ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወልዶ 33 ዓመተ ከ3 ወር በምድር ላይ ተመላልሦ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሰውን ልጅ በደሙ የዋጀው ኢየሱስ ክርስቶስ ትንቢት የተነገረለት ሱባዔ የተቆጠረለት መሆኑን አምነው በሰው ካልተጠመቁ በስተቀር አብርሃም አባታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሚለው እምነት ብቻ አምነው ጌታን በሰቀሉት አይሁድ መንገድ የሚጓዙ ከሆነ እንደማይድኑ በመሲሕ አምነው በስሙም ከተጠመቁ ግን እንደ ሚድኑ ሊያስተምራቸው ስለፈለገ የጌታን ስም ለይቶ ጠራ፡፡ በዚህም የጌታን አዳኝነትና መሲሕነት አምነው እንዲቀበሉ በአጽንዖት መናገሩ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ሐዋርያት ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ቤዛ የሆነልንን ጌታ ሰው ሁሉ አምኖ እንዲድን በየሄዱበት የጌታን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት አሰተምረዋል፡፡ የስብከታቸው ማዕከል የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ክህደቱ ጸንቶ የነበረው በጌታ የባሕርይ አምላክነት ላይ ነበርና፡፡ በዚህ የተነሣ የእርሱን አዳኝነትና የባሕርይ አምላክነት ለማሳመን ጌታን የስብከታቸው ማዕከል አደረጉ፡፡
«ውሳኔዎቻችን ወረቀት ውጧቸው እንዳይቀሩ የሚያስተገብር አስፈጻሚ ያስፈልጋል»
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ያው በሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጵጵስናዬን ይዤ እንድቀጥል ተወስኗል፡፡ በፊትም የቆመ ነገር የለም፡፡ የእርስ በርስ ብጥብጥ ስለነበረ ቅዱስ አባታችን እዚህ ቆይ ስላሉኝ ትንሽ እዚህ ቆይቼ ነበረ፡፡ አሁንም ሥራችንን ከቀጠልን ልንሠራቸው ያሰብናቸው ነገሮች አሉ፡፡ የስብከተ ወንጌሉን አገልግሎት ቅድሚያ ሰጥተን፣ ካህናትን እያሠለጠንን ሕይወት ለዋጭ የሆነውን ትምህርተ ወንጌል ለማስፋፋት ነው የምንሠራው፡፡ ሁለተኛ ልማት ላይ እናተኩራለን፡፡ በቀበሌ ኪራይ ላይ ያለውን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለማሠራት ዕቅድ አውጥተናል፡፡ ሦስተኛ የተጀመረ ማሠልጠኛ አለ፤ አዳሪ ተማሪዎችን ቁጥራቸውን በማሳደግ ጥራት ያለውን ትምህርት ለመስጠት አቅደናል፡፡ ከዚህ በተረፈ እርቅና ሰላምን በመስበክና በማስታረቅ ሰላም እንዲመጣ መጣር ዋናው ዕቅዳችን ነው፡፡ ይህን ከሁሉ ቀድመን የምንፈጽመው ይሆናል፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም የለምና፡፡ ወንጌል ሰላም ነው፣ ትህትና ነው፣ አንድነት ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ያደረገ ሰላምን ለመስበክ እንጥራለን፡፡ እርቅና ሰላሙ በተግባር መገለጥ ያለበት በመሆኑ ይህንኑ በስፋት እንገባበታለን፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- ይህንን ለመፈፀም ከምእመናኑም ሆነ ከአገልጋዮች ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ምእመናንና ካህናት ሁሌም ኅብረት መፍጠር አለባቸው፡፡ ካህናት በጸሎታቸው ምእመናን በገንዘባቸው በሙያቸው፣ በጉልበታቸው ልማትን ማፋጠን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የተዘረዘሩትን የልማት ዕቅዶች እውን የምናደርገው ኅብረት፣ ፍቅርና አንድነት ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተመሠረተችው በምእመንና በካህናት ነው፡፡ ካህናት ስንል ብፁዓን አባቶችም በዛ ውስጥ አሉ፡፡ ስለዚህ ኅብረት እንዲኖር መጸለይ፣ መስማማት፣ መታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሁከት ስለነበረ ምንም ሳናለማ ነው የቆየነው፡፡ እርስ በእርስ መስማማቱ ጠፍቶ ነበር፡፡ እኔም ከተመደብኩ ጀምሮ ለማስታረቅ ብዙ ሞከርኩኝ ችግሩ እዛ አካባቢ ሳይሆን ከሌላ አካባቢ የተለኮሰ ስለሆነ በቀላል ሊበርድ አልቻለም፡፡ እዛ ብቻ ቢወሰን ኖሮ ያን ያህል አያስቸግርም ነበር፡፡ ዘርፍ ያለው፣ ሽቅብ ቀንድ ያለው፣ የሚያድግ፣ ቁልቁለትም አቀበትም ያለው ስለሆነ ብዙ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያ እንዲቀር ነው ጸሎታችን፡፡ ለዚህ ኅብረት ያስፈልጋል፤ ቤተ ክርስቲያናችን መለያየትን አትወድም፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዐይኖችም እጆችም እግሮችም ሁሉም ሕዋሳት ተባብረው እንዲሠሩ አስተምሮናልና፣ ሳይንሱም ያዘናል፡፡ ይህን አንድነት እንድናገኝ እንጸልይ፡፡ ችግራችንን እንወቅ፣ ከባድ የሆነ አደጋ እንደከበበን ዐውቀን እንጠንቀቅ፣ ይህ አደጋ መለያየት መሆኑን ተገንዝበን እንንቃ፡፡ ስለዚህ መለያየታችንን በትዕግሥትና በእርቅ ማስወገድ ሐዋርያዊ ሥራ፣ ቤተ ክርስቲያናዊ ሥራ፣ ሕዝባዊ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በቀጣይ በአካባቢው ሰላም አንድነትና ሥርዓት ተጠብቆ እንዲሔድ ያስችላል የሚል እምነት አለዎት?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ሊቃውንት በቃለ ወንጌል ለማረጋጋት፣ ሰላም ለመስበክ ይሔዳሉ፡፡ እነርሱ ፈጽመው ከተመለሱ በኋላ ሥራችንን ለመቀጠል እንሔዳለን፡፡ ምእመናኑ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ከእኔ ጋር ናቸው፡፡ እነዛም ወንድሞቼ ልጆቼ ናቸው፡፡ አለመግባባት ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ የአምላካችን ፈቃድ ከሆነ ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡ እና ቅዱስ ሲኖዶስ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሰላም፣ አንድነት እንዲሰፍን ጸሎቱም ሥራውም ስለሆነ የታሰበው ይፈጸማል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በደቡብ አካባቢ ትንሽ ስለሆንን ሌትም ቀንም እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ይፈልጋል፡፡ ይህ ፍላጎት እንዲሟላ እግዚአብሔር እንዲረዳን ከልብ እንጸልያለን፡፡
ስምዐ ጽድቅ፡- እርስዎ በቅዱስ ሲኖዶሱ አንጋፋ አባት እንደመሆንዎና በአገልግሎትም ረጅም ዘመን እንደ መቆየትዎ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን አንጻር የሲኖዶሱን ውሳኔዎች አፈጻጸም ካለፉት ዓመታት ጋር እንዴት ያነጻጽሩታል? የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮም ካለ ቢያካፍሉን?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- «ሲኖዶስ» በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መሠረት የሐዋርያትን ሲኖዶስ ተከትሎ የሚሔድ ነው፡፡ ከሐዋርያት ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመሰለው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ውሳኔ ደግሞ ይግባኝ የለውም፡፡ ግን ሲኖዶስን የሚያጅቡ ፍቅር፣ ጸሎት፣ ሰላም፣ ትህትና፣ ይቅርታ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ ተላብሶ ወንጌል እንዲሰብክ የሚወስን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማዋን ሥርዓቷን የሚጠብቅ ነው፡፡ ምእመናን በጎቿን የሚጠብቅ፣ የሚያስጠብቅ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከቀደምት ጊዜያት ጀምሮ ውሳኔ ይወሰናል ነገር ግን ውሳኔን ማስፈፀም ላይ ችግር አለ፡፡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች ላይ አስፈጻሚ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሲኖዶሱን ውሳኔ ከፓትርያርኩ ጎን ሆኖ የሚያስፈልጽም አካል ያስፈልጋል፡፡
ውሳኔዎቻችን ወረቀት ውጧቸው እንዳይቀር በተግባር የሚያስፈጽም ታላቅ ኃይል የለንም፡፡ ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ጋር ተባብረው የሚሠሩ ቢያንስ ዐሥራ ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት አስፈጻሚ አካል ያስፈልጋል፡፡
የራሺያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ የሆነበት ምክንያት ከፓትርያርኩ ጋራ ዐሥራ ሦስት አባላት ያሉበት አስፈጻሚ በመኖሩ ነው፡፡ እኔ ዘጠኝ ዓመት እዛ ስቀመጥ ያየሁት ጠንካራ ነገር ይህ ነው፡፡ ምልዐተ ጉባኤው ወስኖ ሲሔድ እነዚህ አስፈጻሚዎች ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ እያንዳንዱ ውሳኔ አይባክንም፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር በሲኖዶሳችን ሊኖር ይገባል፡፡ መወሰን ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ አፈጻጸሙን መከታተል ይገባል፡፡ መፈጸሙን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲኖዶሳችን አስፈጻሚ ክፍል እንዲኖረው ይደረግ ነው የምለው፡፡ በሕገ ሲኖዶስ እየተመራ የሚሠራ ጠንካራ አስፈጻሚ ክፍል ቢያንስ መቋቋም አለበት፡፡ ብዙ ወስነን ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው ተግባራዊ የሚሆኑት፡፡ ያ ስለሆነ ነው አስፈጻሚ ክፍል አስፈላጊ ነው የምለው፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል “በእንተ ስማ ለማርያም” (ስለ እመቤታችን ማርያም ! ) በሚል መሪ ቃል ያሰናዳው በአብነት ትምህርት ቤቶች ዙሪያ ላይ ያተኮረው ብዙኃን የቤተክርስቲያን ልጆች የተሳተፉበት ዐውደ ርዕይ በሲያትል ንዑስ ማዕከል አዘጋጅነት መጋቢት 7 እና መጋቢት 8 2005 ዓ/ም በሲያትል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አዳራሽ ለሕዝብ እይታ ቀርቧል:: 

ዐውደ ርዕዩ ቅዳሜ መጋቢት 7 2005 ዓ/ም በሲያትልና በአቅራቢያው ካሉ ከተሞች በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ የሰባካ ጉባኤ አባላት፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ደመቅ ባለ ሥነ ሥርዓት ተከፍቷል::
በዚሁ ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል መልእክት በዲ/ ተገኔ ተክሉ የቀረበ ሲሆን በመክፈቻው ላይ በተገኙ ካህናትና ተጋባዥ እንግዶች የተለያየ አስተያየት ተሰጥቷል።
ለሁለት ቀን ክፍት ሆኖ የቆየውን ዐውደ ርዕይ ከ300 በላይ ምእመናን የተመለከቱት ሲሆን ከተሰበሰበውን አስተያየት የብዙኃኑን ስሜት የነካ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል። ዓውደ ርእዩን የተመለከቱ ምእመናን በዕለቱ ቀረበው ከነበሩት ፕሮጀክቶችን መካከል እየመረጡ የወሰዱ ሲሆን በኦንላይን በተዘጋጀው የልገሳ ድረ ገጽ (http://www.gedamat.org) ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል መልእክት በዲ/ ተገኔ ተክሉ የቀረበ ሲሆን በመክፈቻው ላይ በተገኙ ካህናትና ተጋባዥ እንግዶች የተለያየ አስተያየት ተሰጥቷል።
ለሁለት ቀን ክፍት ሆኖ የቆየውን ዐውደ ርዕይ ከ300 በላይ ምእመናን የተመለከቱት ሲሆን ከተሰበሰበውን አስተያየት የብዙኃኑን ስሜት የነካ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል። ዓውደ ርእዩን የተመለከቱ ምእመናን በዕለቱ ቀረበው ከነበሩት ፕሮጀክቶችን መካከል እየመረጡ የወሰዱ ሲሆን በኦንላይን በተዘጋጀው የልገሳ ድረ ገጽ (http://www.gedamat.org) ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
በዚህ ክፍል ስለ አብነት ት/ቤት ከስሙ ትርጓሜ ጀምሮ፣ አብነት ት/ቤት ምን ማለት እንደሆነ፣ ምን አይነት ትምህርት በውስጡ እንደሚያጠቃልል፣ እንዴት እንደተጀመረ፣ በኢትዮጵያ ስለነበሩ እና ስላሉ የአብነት ት/ ቤቶች ያሳየ ክፍል ነው።
አብነት ማለት አባትነት ማለት ሲሆን በአብነት ትምህርት ውስጥ መምህሩ በእውቀት አርአያነት፥ ተማሪው ደግሞ በትህትና አርአያነት ልክ እንደ አባት መምህሩ ለትውልዱ ተማሪው ደግሞ ለጓደኞቹ እና በአካባቢው ለሚኖረው ማኅበረሰብ በህይወቱ በማስተማር አብነት እንደሚሆን ተገልጿል።
የአብነት ትምህርት ጀማሪው እግዚአብሔር አዳምን በቃል በማስረዳት እንደጀመረው፣ ከዛም በሙሴ በጽሁፍ እንደተጠናከረ፣ በመቀጠልም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባር እንዳጸናው ተገልጿል።
ጥንታውያን የአብነት ት/ቤቶችም በትእይንቱ ላይ ሰፊ ሽፋን ያገኙ ሲሆን፥ መቼ እንደተመሰረቱ፣ በአብነት ትምህርት ላይ የነበራቸው እና ያላቸው ፋይዳ በሰፊው ተገልጿል። እንዲሁም እነኝህ የአብነት ት/ቤቶች ያፈሯቸው ታላላቅ ሊቃውንት እንደ አለቃ አያሌው ታምሩ : አለቃ አካለወልድ እንዲሁም ከእነ ቅዱስ ያሬድ ጀምሮ እነማን እንዳስተማሩባቸው ተገልጿል።
2. የአብነት ት/ቤቶች የሥርዓተ ትምህርት አደረጃጀት
3. የአብነት ት/ቤቶች አስተዋጽኦ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሀገር
የአብነት ት/ቤቶች ለቤተክርስቲያን ታላላቅ መምህራን እና ሊቃውንትን በማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የተብራራ ሲሆን፣ ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም መኩሪያ የነበሩ እነሎሬት ጸጋዮ ገብረ መድኅን እና ሃዲስ ዓለማየሁን የመሳሰሉ ታላላቅ ሰዎች ሰዎችን እንዳፈሩ ተገልጿል።
በዚህ ክፍል ውስጥ የሼክስፒር ሶኔት የሚባለው በለ 14 መስመር የቅኔ ስልት ከቤተክርስቲያን የቅኔ ስልት ጋር በማነጻጸር የቤተክርስቲያን የቅኔ ስልት በተሻለ ሁኔታ ሃሳብን ለመግለጽና ለማመስጠር እንደሚያገለግል ተብራርቷል።
4. አኗኗር በአብነት ት/ቤት
በተለይ ተማሪው ምግቡን ለማግኘት ከውሻ፣ ከተፈጥሮ እና ከበሽታ ጋር ምን ያህል ግብ ግብ እንደሚገጥም በአብነት ት/ቤት ሕይወት ባለፉ ሊቃውንት እና የአብነት ተማሪዎች የቪዲዮ ምስክርነት የተገለጸበት ሁኔታ ልብን የሚነካ ነበር።
5. የአብነት ት/ቤቶች ያጋጠሙአቸው ዋና ዋና ችግሮች እና መንስኤዎቻቸው
በዚህ ክፍል ውስጥ፣ እነኝህ ለቤተክርስቲያን እና ለሃገር ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሊቃውንት መፍለቂያ የሆኑ የአብነት ት/ቤቶች በአሁኑ ሰዓት የተጋረጠባቸውን ፈተናዎች በተጠኑ መረጃዎች፣ በፎቶግራፍ እና በቪዲዮ በተደገፈ ሁኔታ ለታዳሚው የቀረበ ሲሆን፣ የተማሪውን እና የመምህራኑን ቸግር የሚያሳዮ ቪዲዮዎች ሲቀርቡ በትዕይንቱ ላይ የተገኙ አንዳንድ ምእመናን ሃዘናቸውን መቆጣጠር ተስኖአቸው ሲያለቅሱ ታይተዋል።
በዚህ ክፍል ውስጥ መፍትሄ እንዲሰጥ ሊረዳ ይችላል በሚል የችግሮቹ መንስኤዎች በሰፊው ተብራርተዋል። ከመንስኤዎቹም ውስጥ የምእመናን አቅም ማነስ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ በዘመናዊው የትምህርት ሥርዓት የአብነት ትምህርቱን አስተዋጽኦ ያለማገናዘብ ተጠቅሰዋል።
6. የአብነት ትምህርት ቤቶች ነገ
አሁን በአብነት ት/ቤቶች ላይ ያጋጠመው ችግር እንዳለ ከቀጠለ በቤተ ክርስቲያን እና በሃገር ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ምን እንደሆነ በዚህ ክፍል የተብራራ ሲሆን፣ በችግሩ ምክንያት ከፊታችን የተጋረጠውን አደጋ እንዳይከሰት ለመከላከል በዚህ የትዕይንት ክፍል ውስጥ የመፍትሔ ሃሳብ ይሆናሉ የተባሉ ሃሳቦች ተጠቁመዋል። መፍትሄዎቹም ተማሪዎቹን በተመለከተ፣ መምህራኑን በተመለከተ፣ ገዳማቱ እና አድባራቱን፣ የመማሪያ ቁሳቁስን በተመለከተ በሚል እንዲሁም የትምህርት ሥርዓቱን በተመለከተ በዝርዝር ቀርበዋል።
7. ማኅበረ ቅዱሳን ለአብነት ት/ቤቶች ያደረገው እና እያደረገ ያለው አስተዋእጽዎ
በዚህ ክፍል ውስጥም በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ገዳማትን በቀላሉ በአንድ ጊዜ ስጦታ ወይንም በየወሩ በሚቆረጥ ስጦታ ለመርዳት የሚያስችለው ድረ ገጽhttp://www.gedamat.org ተዋውቋል።
ባጠቃላይ “በእንተ ስማ ለማርያም” በሚል የተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ለሀገርም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት የአብነት ትምህርት ቤቶች በቀጣይና ዘመኑን በዋጀ መንገድ ሊቀጥሉ የሚችሉበትን ስልት መቀየስና አስፈላጊ መሆኑን ያመላከተና ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመሆን በስፋት መሥራት እንደሚገባ ያመላከተ ነበር ::